እሬቻ የምስጋና ክብረ በአል ቀን!
Yoseph Mulugeta Baba Ph.D., Onkololeesa 3, 2019

An Irreecha gathering in 1903 at Lake Hora Bishoftu.
እሬቻ በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ እንደ ቅዱስ በዓል ይከበራል። እሬቻ በዓል ለዋቃ ጉራቻ ምስጋና የሚሰጥበት ቀን ነው። የመልካም ነገሮች ሁሉ ምንጭ ዋቃዮ ነው። ሕዝቡ ለዚህ መልካም ስጦታ ከልብ የመነጨ ምስጋና ለአምላኩ የሚያቀርብበትና “የዋቃዮ ስጦታ ተመልሶ ለዋቃዮ የምሰጥበት ቅዱስ በአል ነው” ብለው ከልቡ ያምንበታል። ስለዚህ እሬቻ ማለት “ስጦታ” ማለት ነው።
በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ለምለም ሣር የሰላምና የብልጽግና ምልክት በመሆኑ፣ በእሬቻ በዓል ላይ የሚሳተፈው እያንዳንዱ ግለሰብ፣ ይህንን ለምለም ሣር በሁለት እጆቹ በመያዝ አምላኩን ያመሰግናል። ከሁሉም በላይ ክረምቱን ከበረዶ፣ ከከባድ ነፋስ፣ ከጎርፍና ከውርጭ የታደጋቸውን ታላቅና ቅዱስ አምላካቸውን አንድ ላይ ሆኖ ያመሰግናሉ። መኸሩንና አስመራውን ደግሞ እንድባርክላቸው ወደ ፈጣሪ ይጸልያሉ። ስለዚህ የእሬቻ በዓል ከጨለማ ወደ ብርሃን ላሻገረ አምላክ የሚሰጥ የክብር ዋጋ ነው።
ሀገር በቀል የሆኑ የእምነት በዓላትን የመገንዘብና የማብራራት ችግር ያለባቸው ኢትዮሮፒያንስ (Westernized Ethiopians) ግን፣ የእሬቻ በዓልን በተሳሳተ መንገድ ሲረዱና ሲተረጉሙ ይታያሉ። ለምሳሌ፤- በበዓሉ ላይ የሚደረገውን የአምልኮ ሥነ-ሥርዓት በመመልከት፣ ሕዝቡ ዋቃዮን ሳይሆን ውሃውን አልያም ሰይጣንን “እንደሚያመልክ” አድርገው ይረዳሉ። ኦድላይ ሶቴቪንስን “በአቶሚክ ቦንብ ውስጥ ሰይጣን የለም፣ በሰዎች ልቦና እንጂ” እንዳለ ሁሉ፣ ሰይጣን በእነዚህ ሰዎች አይምሮ ውስጥ እንጂ በውሃ ውስጥ አይኖርም። ሰይጣን ዳክዬ ወይም ጉማሬ አይደለም—ካልጠፋ ቦታ ውሃ ወስጥ አሁን ምን ይሰራል! ባይሆን የሰይጣን ትክክለኛ አድራሻና ማደሪያ የሰው ልቦና ነው—ስለዚህ፣ኢትዮሮፒያንስ ሰይጣንን ልቦናቸው ውስጥ ይፈልጉት!
በተቃራኒው ውሃ የሕይወት ምልክት ነው። ለዚህም ነው ውሃና ልምላሜ እንደ ዋቃዮ ስጦታ የሚታዩት። ያለ ውሃ ሕይወት ቀጣይነት የለውም። ውሃ ዋቃዮ ለፈጠራቸዉ ልጆቹ የሰጠ ፀጋ ነው። ድሪቢ ደምሴ ቦኩ እንዳለው፤ “ኦሮሞ፣ ወንዝ፣ ጫካና ተራራ ይወዳል፤የተፈጠረበትና ፍቅር ያገኘበት ስለሆነ በየዓመቱ ለምለም ሣርና የፀደይ አበባ ይዞ ለእሬቻ ወንዝ ውሃ ዳርቻ በመሄድ፤ ተራራ ላይ በመውጣት፤ ለፈጣሪው ምስጋና ያቀርባል። በጤና፣ በሰላም፣ ለሰውና ለከብት እርባታ እንዲሰጠውም ይጸልያል።”
በሌላ በኩል #እሬቻ ሃይማኖታዊ ክብረ በአል እንጂ ሃይማኖት አይደለም። ለምሳሌ፡- ፋሲካ፣ አረፋ፣ ጥምቀት፣ ገና ወዘተ ሃይማኖታዊ በዓሎች ናቸው እንጂ በራሳቸው ሃይማኖት አይደሉም፡፡ የኦሮሞ ሀገር በቀል ሃይማኖት #ዋቄፋና ተብሎ ይጠራል። Waaqa ማለት እግዚአብሔር ማለት ሲሆን፣ Faana ማለት ደግሞ መከተል ማለት ነው። ትርጉሙም ፈጣሪን/እግዚአብሔርን መከተል ማለት ነው።
ለኦሮሞ ሕዝብ ዋቃ የሁሉ ነገር አስገኝ፣ የማይጠፋ፣ የማይለወጥ፣ ቋሚና ዘለዓለማዊ ነው። ነው። የሁሉም ነገር ምንጭ ዋቃ ነው። ዋቃ ምሉዕ በኩለሄ (omniscient)፣ ሁሉን ቻይ (ominipresent)፣ ዘላለማዊ (eternal)፣ ፍጹም (absoulute)፣ እና ገደብ የሌለው (infinite) ነው። ዋቃ ፍጹም አንድ ነው። ሀገር-በቀሉ የኦሮሞ ሥነ-እውቀት ዋቃን የሚገልጽበት መንገድ ጥንቃቄ የተሞላበት ነው። በማንኛውም ጊዜና ቦታ ዋቃ የሚለው ቃል ሲጻፍም ሆነ ሲነገር ‹‹ጉራቻ›› የሚለውን ቅጽል አስከትሎ ነው። ቀጥተኛ ትርጉሙም ‹‹ጥቁር›› ማለት ሲሆን በኦሮሞ ንጽረተ-ዓለም ጥቁርነት የልዕልና ምልክት ብቻ ሳይሆን፣ የዋቃን ቀዳማዊነት (Originality) የሚገልጽ ነው። ጥቁርነት የዋቃ ምንነት በሰው አህምሮ ሊደረስበት የማይቻል እጅግ ፍጹም ምስጢር መሆኑን የሚገልጽ ጽንሰ–ሐሳብ ነው።
እንግዲህ እሬቻ የሰላምና የእርቅ ጊዜንም ስለምያስታውሰን ይህንን በዓል ስናከብር:-
(1ኛ) ለሀገራችንም ዋቃዮ አንድነት፣ ፍቅርና ሠላም እንድያመጣ እንጸልያለን። በተለይ ለሆዳቸው ሳይሆን ለህሊናቸው ብቻ ሲሉ ሕዝባቸውን በቅንነት የሚያገለግሉ ግለሰቦችን ዋቃዮ ሀብታቸውንና ልጆቻቸውን እንድባርክላቸው ወደ ዋቃዮ ጉራቻ እንጸልያልን፤
(2ኛ) በተቃራኒው በሕዝብ ስም የሚነግዱ ሆዳሞች፣ ወንጀለኞች፣ ነፍስ ገዳዮች፣ ሌቦች፣ አጨበርባሪዎች፣ አስመሳዎች…ወዘተ ዋቃዮ የሕዝቡን ለቅሶ ሰምቶ በታላቅ ክንዱ ወደ ፍርድ እንዲያመጣልን ለምለም ሣር በሁለት እጆቻችን በመያዝ ዋቃዮን እንማጸናለን።
(3ኛ) ስለ ድሆች አሰቃቅ ሁኔታ ሳይሆን፣ ስለ “ፔንሲዮን”ና “ዶላሪዝም” አብዝቶ የሚያስቡ የመንግስት ባለስልጣናትና የሃይማኖት አባቶች እንደ አሸን ፈልተዋልና፣ ዋቃዮ የ“ሳፉና ሳፌፋና” ምስጥር እንድገልጥላቸው ለምለም ሣር በሁለት እጆቻችን ይዘን ወደ እርሱ እንፀልያልን፤
(4ኛ) ስለ አይምሮው ሳይሆን፣ ስለ አለባበሱና ሆዱ ብቻ ብዙ የሚጨነቅ ወጣት ትውልድ ተፈጥረዋልና፣ ዋቃዮ ጉራቻ ‹ልብስ› ሳይሆን ‹ልብ›፣ ‹ጋቢና› ሳይሆን ‹ልቦና›፣ ‹ፎቅ› ሳይሆን ‹ሐቅ›፣ ‹ድራፍት› ሳይሆን ‹ድፍረት› እንድሰጣቸው ለምለም ሣር በሁለት እጆቻችን ይዘን ወደ እርሱ እንፀልያልን!
የእሬቻ ቅዱስ በዓል ጸሎትን አንድ ላይ እንጸልያልን፡–
ሀዬ! ሀዬ! ሀዬ!
ሀዬ! የእውነትና የሰላም አምላክ!
ሀዬ! ጥቁሩና ሆደ ሰፊው ቻይ አምላክ!
በሰላም ያሳደርከን በሰላም አውለን!
ከስህተትና ከክፉ ነገሮች ጠብቀን!
ለምድራችን ሰላም ስጥ!
ለወንዞቻችን ሰላም ስጥ!
ከጎረቤቶቻችን ጋር ሰላም ስጠን!
ለሰውም ለእንስሳቱም ሰላም ስጥ!
ከገዳ ባህላችን ከዋቄፋና እምነታችን ጋር አኑርልን!
አንድነታችንን አጠንክርልን!
ትናንሾቻችንን አኑርልን!
ጤነኛና ብልህ ልጆች ስጠን!
ወላድ በጤና ትገላገል!
የወለደችውን አሳድግላት!
ሕጻን በእናቱ እቅፍ ይደግ!
ለወላድ ጤናና ዕድሜ ስጣት!
ላልተማረው እውቀት ስጥልን!
ኦ አምላክ አደራጀን!
አደራጅተህ አታፍርሰን!
ተክለህ አትንቀልን!
ፈጥረህ አትዘንጋን!
ክፉውን ያዝልን!
ከወንጀልና ከወንጀለኛ አርቀን!
ምቀኛና ቀናተኛውን ያዝልን!
ከመጥፎ አየር ጠብቀን!
ንጽሕ ዝናብ አዘንብልን!
ያላንተ ዝናብ የእናት ጡት ወተት አይሰጥምና!
ያላንተ ዝናብ የላም ጡት ወተት አይሰጥምና!
ያለንተ ዝናብ መልካው ውሃ አይሰጥምና!
ያላንተ ዝናብ ምድሩ ቡቃያ አይሰጥምና!
ከእርግማን ሁሉ አርቀን!
በአባቱ ከተረገመ አርቀን!
በእናቷ ከተረገመች አርቀን!
እውነትን ትቶ ከሚዋሽ አርቀን!
ከረሀብ ሰውረን!
ከበሽታ ሰውረን!
ከጦርነት ሰውረን!
ልጄ እያሉ አልቅሶ ከመቅበር ሰውረን!
በጥቁር ፀጉር ከመሞት ሰውረን!
በነጭ ፀጉር ከመደህየት ሰውረን!
አርሶ ምርት ከማጣት ሰውረን!
ከሌላ ሰው ጦስ ሰውረን!
ከከፉ ነገር ሁሉ ሰውረን!
ገዳው የሰላም፣ የልምላሜና የድል ነው!
ሀዬ! ሀዬ! ሀዬ!
Posted on October 4, 2019, in Events, Information, News. Bookmark the permalink. Leave a comment.
Leave a comment
Comments 0