ከትብብር ለሕብረብሔር ዴሞክራሳዊ ፌደራሊዝም (ትብብር ) የቀረበ ፖለቲካዊ የመፍትሔ ሀሳብ

በኮቪድ-19 ምክንያት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የገጠመውን ሕገ-መንግሥዊ ቀውስ (አጣብቂኝ) ለማሻገር ከትብብር ለሕብረብሔር ዴሞክራሳዊ ፌደራሊዝም (ትብብር ) የቀረበ ፖለቲካዊ የመፍትሔ ሀሳብ

መግቢያ፡
የደርግ አገዛዝ በ1983 ካከተመ በኋላ ኢሕአዴግ የሚመራዉ መንግሥት ለ27 ዓመታት የመንግሥትን ስልጣን፣ ሕግ አዉጪዉ፣ የሕግ አስፈጻሚዉንና የፍትሕ ተቋሙን ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር በአንድ ፓርቲ አገዛዝ ሥር ሀገሪቷ እንድትወድቅ አድርጓታል። በዚሁ ኢሀአድግ የበላይነት በሰፈነበት አምባገነናዊ አገዛዝ ይህ ነዉ የማይባል የሰብዓዊ መብት ጥሰትና በጥቂቶች ከፍተኛ የኢኮኖሚ ምዝበራ በኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ ተፈጽሞዋል። ይሄን አስከፊ የሆነ አምባገነናዊ ሥርዓት ላለመቀበል የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ከፍሎቹ በትጥቅ ትግል፡ በጋራም ሆነ በተናጠል ፣ የተለያዩ ሕዝባዊ አመጾች በተለያዩ የሀገሪቷ ክፍሎች ሲያደርጉ ቆይተው ሕዳር 2007 በኦሮሞ ወጣቶች በኦሮሚያ የተቀሰቀሰዉ ሕዝባዊ አመጽ ወደመላዉ የሀገሪቷ ክፍሎች ተስፋፍቶ በታህሳስ ወር 2010 ኢሕአዴግ እራሱን በጥልቅ ተሃድሶ ማሻሻል እንዳለበት አምኖ እንዲቀበል ማስገደዱ ይታወሳል። የዚህ ሕዝባዊ አመጽ በኢሕአዴግ ዉስጥ ለዉጥ ፈላጊ ኃይል ታክሎበት መጋቢት 24 ቀን 2010 ዶ/ር አቢይ አህመድ ወደ ጠ/ሚንስቴርነት እንዲመጡ አድርጓቸዋል።
በጠ/ሚንስቴር ዶ/ር አቢይ አህመድ አመራር ሥልጣኑን የያዘዉ ኃይል ኢትዮጵያ ከአምባገነናዊ አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንደሚያሸጋግር ቃል ገብቶ ክፍተኛ ተስፋና እምነት ተጥሎበት ነበር። ለዚሁም ጠቅላላ ምርጫ ከመድረሱ በፊት የሚያስፈልጉ ሪፎርሞችና የህግ ማሻሻያ ዝግጅቶች ተደርገዉ በምርጫ 2012 ዴሞክራሲያዊ የሆነ ምርጫ ተካሄዶ ሕዝብን የሚወክል መንግሥት እንደሚመሠረት በተስፋ ሲጠበቅ ነበር። ሌሎች በርካታ ተግዳሮቶች ባሉበት ሁኔታ በተጨማሪ በጠቅላላ ምርጫው ዋዜማ ዓለም-አቀፋዊ የሆነ ወረርሺኝ የኮቪድ-19 በሽታ መከሰቱ ምርጫዉ በታቀደለት ጊዜ እንዳይከናወን በማድረግ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ አድርጎታል። ከዚህ የተነሳ በሕገ-መንግሥቱ የምርጫ ድንጋጌ አጣብቂኝ/ቀውስ ወስጥ መግባቱ እጅግ አሳሳቢ ሆኗል። ለዚሁም የችግሩ ተቋዳሽ በመሆን በበኩላችን ከዚህ አጣብቂኝ ለመዉጣት ይረዳል ብለን የሚናምንበትን የመፍትሔ ሀሳብ ይዘን ቀርበናል። ለመፍትሔ ሀሳቡ መነሻ ይሆን ዘንድ ከመጋቢት ወር 2010 ጀምሮ ሀገሪቷ ያሳለፈችዉ ፖለቲካዊና ማሕበራዊ ሂደቱን መዳሰስ እጅግ አስፈላጊ ነዉ ብለን እናምናለን። ለዚሁም የለዉጡን ሂደት ከመጋቢት ወር 2010 ጀምሮ ያጋጠሙትን ችግሮች በመገምገም አሁን ሀገሪቷ ያለችበትን ተጨባጭ ሁኔታ በማጤን ለተጋረጠብን ሕገ-መንግሥታዊ ቀዉስ የመፍትሔ ሀሳብ ማቅረቡ ይበጃል ብለን እናምናለን።
1. የለዉጥ ኃይሉ (Reformist Group) የወሰዳቸዉ ተስፋ ሰጪ እርምጃዎች
በዶ/ር አቢይ አህመድ የሚመራዉ የለዉጥ ኃይል የሚከተሉትን ተስፋ ሰጪ ዉሳኔዎችና እርምጃዎችን ማስተላለፉና መዉሰዱ ይታወሳል። እነሱም፡
1. የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት
2. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማንሳት
3. የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች (ትጥቅ ትግል ሲያካሄዱ የነበሩትንም ጨምሮ) ወደ ሀገር ተመልሰው ህጋዊ በሆነ መልኩ የቆሙለትን ዓላማ እንዲያራምዱ ሁኔታዎችን ማመቻቸት
4. በሀገሪቷ ዉስጥ የዴሞክራሲን መሠረት ለመጣል ማነቆ ሁነዉ የነበሩትን የሽብርተኝነት፣ የሚዲያና የሲቭል ድርጅቶችን አዋጅ ማሻሻል
5. የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድን አወቃቀር በአዲስ መልክ ማደረጀትና የቦርዱ ኃላፊዎችን መለወጥ
6. በአጠቃላይ አቃቤ ሕግ ሥር የሕግና ፍትሕ አማካሪ ም/ቤትን ማቋቋም
7. የማዕከላዊ እሥር ቤትን መዝጋት
8. ከሀገር ዉጪ ሆነው ሲሰሩ የነበሩትን የመገናኛ ብዙሃን ወደ ሀገር ቤት ገብተው እንዲሠሩ ማድረግና ታግደዉ የነበሩትን ድህረ-ገጾች ለተጠቃሚዎች ክፍት እንዲሆኑ ማድረግ
9. በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የነበረዉን የፀጥታ ችግር በእርቅ መፍታትና የመሳሰሉት ናቸዉ።
2. የለዉጥ ሂደቱን ያጋጠሙት ችግሮች
የለዉጡን ሂደት የገጠሙት ችግሮች በሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል። እነሱም፡ አጠቃላይ እና በተለይ ደግሞ ኢሕአዴግ/ብልጽግና ፓርቲን እንደ ገዢ ፓርቲነቱ ያጋጠሙት ተግዳሮቶች ማለት ይቻላል።
አጠቃላይ ችግሮች፡
በሀገሪቱ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ተቀራራቢ አመለካከት አለመኖራቸውና መቻቻል ባለመኖሩ መንግሥታዊ አወቃቀር (State-Structure and Nation-Building) ላይ ብሔራዊ መግባባት አለመቻሉ፣ እንዲሁም የብሔር ብሔረሰቦች ብሔረተኝነት እና የኢትዮጵያዊ ዜግነትን አዋህዶና አጣጥሞ መሄድ ካለመቻል የተነሳ አብሮ ከመሥራት ይልቅ ርስ-በርስ የመጣራጠር ስሜቶች መጉላታቸዉ፣ በተለይ ደግሞ በረዥም የሕዝቦች ትግል የተገኘዉንና ተጨቁነናል ብለው የሚያምኑ ሕዝቦችን በተወሰነ ደረጃ ጥያቄያቸዉን የመለሰዉንና ህገ-መንግሥታዊ እዉቅናም ያገኘዉን ህብረ-ብሔራዊ ፌዴራሊዝምን አፍርሶ ወደኋላ በመመለስ በአሮጌዉ መንግሥታዊ ሥርዓትና አወቃቀር ለመተካት የሚደረግ ጥረት ትልቅ ልዩነት በመፍጠሩ ያለዉን አቅምና ዕዉቀት በአንድ ላይ ከማምጣት ፈንታ መጠላለፍ ካሉት ተግዳሮቶች ኣንዱ ሆኗል።
ኢሕአዴግ/ብልጽግና እንደ ፖለቲካ ፓርቲ እና መንግስት፡
የሚከተሉት ችግሮች ኢሕአዴግ/ብልጽግና ፓርቲን እየገጠሙ መሄዳቸዉ የአጠቃላይ ችግሮች አካል ነዉ። እነሱም፡
• ዉስጣዊ የሥልጣን ሽኩቻ (Internal power struggles within the EPRDF)
• ይህ ችግር የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች በመካከላቸዉና እያንዳንዳቸዉም በዉስጣቸዉ ያላቸዉ ችግር መሆኑና ይህ ችግር በሂደት ትሕነግ/TPLF ሙሉ በሙሉ ከሌሎች ኢሀአድግ አባል ድርጅቶች በኋላ ከብፓ/PP እራሱን እስከማግለል ኣድርሶታል። በኢሕአዴግ/በብልጽግና ፓርቲና በመንግሥት መካከል ልዩነት እንዳልነበረ በመንግሥት ሥራ አፈጻጸም ላይ ይንጸባረቅ ነበር።
• የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት፡
• ባጠቃላይ አሁንም ድረስ በተላያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች የሰብዓዊ መብቶች ኣለመከበር በስፋት ይታያሉ። በሰላማዊ ዜጎች ላይ በሚካሄዱ እስራትና ግድያዎች በርካታ መሆናቸዉ፣ የበርካቶች ተፎካካሪ ፖርቲዎች አባላትና ደጋፊዎች እንዲሁም የአመራር አባላት ታስረው እስካሁን እስር ቤት ዉስጥ የሚግኙ መሆናቸዉ፣ ለአብነት፡ የኦብነግ፣ የአገዉ ብሔራዊ ሸንጎ፣ የኦነግ፣ የቅማንት ዴሞክራሲያዊ ድርጅት፣ ፣ የኦፌኮ፣ የሲዳማ፣ የጋምቤላ፣ የአብን …ወዘተ። በተጨማሪም የፖለቲካ ድርጅቶች ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው መስራት አለመቻል በተለይም የታችኛው የገዢ ፓርቲ መቀቅርና የመንግስት አካላት በፓርቲዎች ላይ የሚያደርሱት ወከባ መበራከት አሳሳቢ ጉዳይ መሆኑ።
• በተለያዩ ሕዝቦች መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶች
• በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ በአማራ፣ በቤንሻንጉል-ጉሙዝ እና በሶማሌ ክልሎች ኣንዲሁም በሌሎች አከባቢዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ ሰላም መታጣት
• የወጣቶች ሥራ አጥነትን ማቃለል ኣለመቻሉ፣ በአንፃሩ የለዉጡ ዋነኛ ኃይል የነበረዉ ይህ ሥራ-ኣጥ ወጣት በመንግሥት ላይ የነበረዉ ከፍተኛ ተስፋ መመናመኑ።
• የኢኮኖሚ ዕድገት ማሽቆልቆል፣ መህበራዊ ቀውሶች ከግዜ ወድ ግዜ መበራከት፣ የአከባቢ ጥበቃና የተፈጥሮ ሀብቶች ውድመት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መሆናቸው
• በትግል ላይ የነበረዉን የሰዉ ኃይል በአግባቡ በሥርዓቱ ዉስጥ ማቀፍ ኣለምቻሉ፣ ((Reintegration of armed (combatants) lack of proper demobilization, rehabilitation and reintegration processes.
• ለ2012ቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ዝግጅት እያደረገ ባለበት የኖቬል ኮሮና ቫይረስ (COVID-19) በሽታ መከሰቱ፣
3. ኮቪድ-19 ፣ የ2012ቱ የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ እና ህገ-መንግሥታዊ ተግዳሮቱ (challenges of the constitution/Constitutional crises)
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኮቪድ-19 ምክንያት ለነሐሴ መጋቢት 22 ቀን 2012 ለነሓሴ 23 ቀን 2012 6ኛ ጠቅላላ ምርጫ በታቀደለት የጊዜ ሰሌዳ ማካሄድ አልቻልኩም ስል ወስኖ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት መፍትሔ እንድፈለግለት ለምክር በቱ ማስተላለፉም ይታወሳል።
ስለዚህ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት በህገ-መንግሥቱ መሠረት የተመረጠበትን አምሥት ዓመት የጊዜ ገደብ በህገ-መንግሥቱ መሠረት ምርጫ ተካሂዶ ሥልጣኑን ለሚመረጠው አድሱ ም/ቤት ለማስተላለፍ በተፈጠረዉ ችግር ምክንያት የማይቻል በመሆኑ ህገ-መንግሥታዊ ቀዉስ ዉስጥ ልገባ ስለሆነ የተፈጠረዉን ሁኔታ በመገምገም የመፍትሔ ሀሳብ ማመንጨትና ማቅረብ እንደ ፖለቲካ ድርጅት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።
3.1 በህገ-መንግሥቱ ዉስጥ ካሉት አንቀጾች መካከል በምርጫ መራዘሙ ምክንያት ለጥሰት የተጋለጡ አንቀጾች
በመሰረቱ ከህገ-መንግሥቱ አንቀጾች አንዱንም መጣስ ህገ መንግስታዊ አይደለም። ባሁኑ ሁኔታ ይህ ጠቅላላ ምርጫ በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ዉስጥ ካልተደረገ ከሀገሪቱ ህገ-መንግሥት አንቀጾች ዉስጥ ልጣሱ ነው የሚንላቸዉን ወሳኞቹ አንቀጾች የሚከተሉት ናቸዉ፡
• አንቀጽ 1: የኢትዮጵያ መንግሥት ስያሜ ራሱ እንደሚያመለክተዉ “ይህ ሕገ መንግሥት ፌዴራላዊና ዴሞክራሲያዊ የመንግሥት አወቃቀር ይደነግጋል፡፡ በዚህ መሰረት የኢትዮጵያ መንግሥት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ በሚል ስም ይጠራል፡፡” ይህ ዴሞክራሲያዊ የመንግሥት ምሥረታ ልኖር የሚችለዉ ቢያንስ ወቅታዊ ምርጫ በየጊዜዉ በማድረግ ዜጎች የሚወክላቸዉን ሲመርጡ ነው።
• አንቀጽ 54. 1. “የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፤ ሁሉ አቀፍ፣ ነጻ ፣ ቀጥተኛ፣ ትክክለኛ በሆነና ድምጽ በሚስጥር በሚሰጥበት ሥርዓት በየአምስት ዓመቱ በሕዝብ ይመረጣሉ፡፡” ይህ አለመሆኑ ሕዝቡን የሚወክል የተወካዮች ም/ቤት አለመኖርን ያመላክታል። በዚሁ መሠረት አሁን ያለዉ የም/ቤቱ የሥራ ዘመን ካለቀ በኋላ የሚወጡት አዋጆችና ድንቦች ህጋዊነት አይኖራቸዉም።
• አንቀጽ 58.3 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚመረጠው ለአምስት ዓመታት ነው፤ የሥራ ዘመኑ ከማብቃቱ ከአንድ ወር በፊት አዲስ ምርጫ ተካሂዶ ይጠናቀቃል፡፡ ይህ አንቀጽ እንደሚደነግገዉ የአምስት ዓመት ጊዜዉን የማራዘም ፍንጭ ኣያሳይም።
• አንቀጽ 61. 3 የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት በክልል ምክር ቤቶች ይመረጣሉ፤ የክልል ምክር ቤቶች በራሳቸው ወይም በቀጥታ በሕዝብ እንዲመረጡ በማድረግ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባል እንዲወከሉ ያደርጋሉ፡፡ የክልሎች ም/ቤት አባላት ምርጫም ባለመከናወኑ ምክንያትም የፌዴሬሽኑ ም/ቤት መቋቋም አይቻልም ማለት ነዉ።
• አንቀጽ 67. 2 የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት የሥራ ዘመን አምስት ዓመት ይሆናል፡፡ ይህም አንቀጽ እንደሚደነግገዉ የአምስት ዓመት ጊዜዉን የማራዘም ፍንጭ ኣያሳይም።
• አንቀጽ 72. 2 ጠቅላይ ሚኒስትሩና የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተጠሪዎች ናቸው፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባላት በመንግሥት ተግባራቸው በጋራ ለሚሰጡት ውሳኔ የጋራ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ የተወካዮች ም/ቤት ህጋዊ እስካልሆነበት ጊዜ ድረስ በአንቀጹ ዉስጥ የተጠቀሱት አካላት ተጠሪነታቸዉ ለማን እንደሚሆን አጠያያቂ ነዉ።
• አንቀጽ 72. 3 በዚህ ሕገ መንግሥት መሰረት በሌላ አኳኊን ካልተወሰነ በስተቀር የጠቅላይሚኒስትሩ የሥራ ዘመን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሥራ ዘመን ነው፡፡ ይህም አንቀጽ እንደሚደነግገዉ የጠ/ሚንስቴሩ የሥራ ዘመን ከአምስት ዓመት በላይ ልሆን እንደማይችል ይደነግጋል።
• አዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀጽ 7.1 ጠቅላላ ምርጫ በየአምስት ዓመቱ የሚካሄድ የህዝብ ተወካዮች እና የክልል ምክር ቤቶች አባላት ምርጫ ነዉ።
ይህ በኮቪ-19 ምክንያት ባለመከናወኑ በዴሞክራሲያዊ መንግሥት አመሠራረት ላይ ተመርኩዞ የወጣዉን አዋጅ አለመተግበሩ ለአጠቃላይ ህገ-መንግሥታዊ ቀዉስ ሀገሪቷን ይዳርጋታል።
3.2 የመንግሥትን የሥልጣን ዘመን ለማራዘም ዕድል የሚሰጥ የህገ-መንግሥት አንቀጽ አለመኖሩ
ሀ) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ
አንቀጽ 93. 1. ለ) የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም ወይም የሕዝብን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት የክልል መስተዳድሮች በክልላቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊያውጁ ይችላሉ፡፡ዝርዝሩ ክልሎች ይህን ሕገ መንግሥት መሰረት በማድረግ በሚያወጧቸው ሕገመንግሥቶች ይወሰናል፡፡ ይህ ሁኔታ በም/ቤቶቹ የሥልጣን ጊዜ ገደብ (አምስቱ ዓመት) ዉስጥ ለሚከሰት እንጂ የጊዜ ገደቡን ለማራዘም አያገለግልም።
ለ) ም/ቤቱን ማፍረስ/መበተን
አንቀጽ 60. 1 ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥልጣን ዘመኑ ከማለቁ በፊት አዲስ ምርጫ ለማካሄድ በምክር ቤቱ ፈቃድ ምክር ቤቱ እንዲበተን ለማድረግ ይችላል፡፡
ይህም ሊሆን የሚችለዉ በተቅላይ ሚንስትሩና በም/ቤቱ የሥልጣን ዘመን ዉስጥ እንጂ ጊዜዉን ለማራዘም ፈጽሞ ኣያገለግልም። በህገ መንግስቱ አንቀጽ 60 የተደነገገው ከመደበኝ ምርጫ በፊት አዲስ ምርጫ ለማካሄድ እንጂ መደበኛውን ምርርጫ ለማራዘም የተደነገገ እንዳልሆነ ግልጽ ነው።
ሐ) የሕገ-መንግሥት ማሻሻያን ማድረግ
አንቀጽ 104 የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሐሳብን ስለማመንጨት
አንድ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሐሳብ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሁለት ሦስተኛ ድምጽ የደገፈው፣ የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት በሁለት ሦስተኛ ድምጽ የደገፈው ወይም ከፌዴሬሽኑ አባል ክልሎች ውስጥ አንድ ሦስተኛው የክልል ምክር ቤቶች በድምጽ ብልጫየደገፉት ከሆነ ለውይይትና ለውሳኔ ለመላው ሕዝብና የሕገ መንግሥቱ መሻሻል ለሚመለከታቸው ክፍሎች ይቀርባል፡፡
አንቀጽ 105 ሕገ መንግሥቱን ስለማሻሻል
አንቀጽ 105. 1 በዚህ ሕገ መንግሥት ምዕራፍ ሦስት የተዘረዘሩት መብቶችና ነጻነቶች በሙሉ፣ይህ አንቀጽ፣ እንዲሁም አንቀጽ 104 ሊሻሻሉ የሚችሉት በሚከተለው አኳን ብቻ ይሆናል፡፡
ሀ/ ሁሉም የክልል ምክር ቤቶች የቀረበውን ማሻሻያ በድምጽ ብልጫ ሲያጸድቁት፣
ለ/ የፌዴራሉ መንግሥት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሁለት ሦስተኛ ድምጽ የቀረበውን ማሻሻያ ሲያጸድቀው፣ እና
ሐ/ የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት በሁለት ሦስተኛ ድምጽ ማሻሻያውን ሲያጸድቀው ነው፡፡
አንቀጽ 105. 2 በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 ከተዘረዘሩት ውጭ ያሉት የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች ሊሻሻሉ የሚችሉት በሚከተለው አኳን ብቻ ይሆናል፤
ሀ/ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት በጋራ ስብሰባ በሁለት ሦስተኛ ድምጽ የቀረበውን ማሻሻያ ሲያጸድቁት፣ እና
ለ/ ከፌዴሬሽኑ አባል ክልሎቸ ምክር ቤቶች ውስጥ የሁለት ሦስተኛ ክልሎች ምክር ቤቶች በድምጽ ብልጫ የቀረበውን ማሻሻያ ሲያጸድቁት ነው፡፡
ለሕገ-መንግሥቱ የማሻሻያ ሀሳብ ለማቅረብ የሚያስፈልጉ ሌሎች ቅድመ-ሁኔታዎቹ ልሟሉ የሚችሉ እንኳ ቢሆን “ለውይይትና ለውሳኔ ለመላው ሕዝብና የሕገ መንግሥቱ መሻሻል ለሚመለከታቸው ክፍሎች ይቀርባል፡፡” የሚለዉን ቅድመ-ግዴታ ለማሟላት በ ኮቪድ-19 ምክንያት ስለማይቻል በዚህ በኩል ያለዉም ዕድል በሩ የተዘጋ ነዉ።
መ) ሕገ-መንግሥቱን ስለመተርጎም
አንቀጽ 83. 1 የሕገ መንግሥታዊ ክርክር ጉዳይ ሲነሳ በፌዴሬሽኑ ምክር ቤት ውሳኔ ያገኛል፡፡
አንቀጽ 83. 2 የፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ በሚያቀርብለት ሕገ መንግሥታዊ ጉዳይ ላይ በሠላሣ ቀናት ውስጥ ውሳኔ ይሰጣል፡፡
ይህ ህገ-መንግሥቱን የመተርጎም ስርዓትም በመሠረቱ የሚመለከተዉ ክርክር ያለባቸው ወይም አወዛጋቢ የሆኑ አንቀጾች በተለያዩ አካላት ለአጣሪ ጉብዔ ስቀርቡ እንጂ ከመሬት ተነስተው አንቀጾችን በመተርጎም ሊሆን አይችልም። የህገ-መንግስቱን አንቀጽ 9 እና አንቀጽ 54ን ማስታረቅም የሚቻልበት መንገድ ኣይታይም።
3.3 ህገ-መንግሥታዊ የመፍትሔ ዳሰሳዉ አጠቃላይ ጭብጥ
ማጠቃለያ፡
1) በኮቪድ-19 ምክንያት ምርጫዉን ማራዘም ግድ ሆኖዋል።
2) ህገ-መንግሥቱን ተከትሎ ምርጫዉን ለማራዘም የሚያስችል አማራጭ ከህገ-መንግሥቱ ዉስጥ ማግኘት አይቻልም። ካሁን በፊት ኢሕአዴግ ለሕዝብ ዉይይትና ዉሳኔ ሳያቀርብ ህገ-መንግሥቱ ላይ ማሻሻያ አድርጎ ነበር የሚለዉ ተሞክሮም (precedence) ተቀባይነት የለዉም።
3) በህገ-መንግሥቱ አንቀጽ 9. 2 ላይ እንደተደነገገዉ “ማንኛውም ዜጋ፣ የመንግሥት አካላት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ሌሎች ማኅበራት እንዲሁም ባለሥልጣኖቻቸው፣ ሕገ መንግሥቱን የማስከበርና ለሕገ መንግሥቱ ተገዢ የመሆን ኃላፊነት አለባቸው፡፡” ይላል። ስለዚህ፣ መፍትሔዉ ለሀገርና ለሕዝቦች ሰላምና መግባባት ሲባል አገርን በሚጠቅም መልኩ በጥንቃቄና በስምምነት ከዉሳኔ የሚደረስበት ልሆን ይገባል።
3.4 ከህገ-መንግሥቱ ዉጪ ሥልጣንን ማራዘም የሚያመጣዉ ችግር
ህገ-መንግሥቱን ባልተከተለ መንገድ በመንግሥት በራሱ ዉሳኔ የሥልጣን ጊዜዉን የሚያራዝም ከሆነ፡
አንቀጽ 9. 3 (በዚህ ሕገ መንግሥት ከተደነገገው ውጭ በማናቸውም አኳን የመንግሥት ሥልጣን መያዝ የተከለከለ ነው፡፡) የሚለዉን መተላለፍ መሆኑና ይህም በሌላ በኩል የሀገሪቱን ህገ-መንግሥት ብቻም ሳይሆን በህገ-መንግሥቱ ዉስጥ በአንቀጽ 9. 4 ላይ የተካተቱትን ዓለም-አቀፋዊ ስምምነቶችንም (9.4 ኢትዮጵያ ያጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የሀገሪቱ ሕግ አካል ናቸው፡፡) መጣስ ይሆናል። ይህም ለምሳሌ፡
በአፍሪካ አንድነት ቻርተር ዉስጥ፥“Chapter 8 Sanctions in Cases of Unconstitutional Changes of Government
Article 23.5 Any amendment or revision of the constitution or legal instruments, which is an infringement on the principles of democratic change of government.”
እንዲሁም፣
“Universal Declaration of Human Rights፥ The Declaration was proclaimed by the United Nations General Assembly in Paris on 10 December 1948
Article 21 .1. Everyone has the right to take part in the government of his country, directly or through freely chosen representatives.
Article 21.3 The will of the people shall be the basis of the authority of government; this will shall be expressed in periodic and genuine elections which shall be by universal and equal suffrage and shall be held by secret vote or by equivalent free voting procedures.”
4. የመፍትሔ ሀሳብ
በየአምስት ዓመቱ የሚደረግ ጠቅላላ ምርጫን በማራዘም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስራ ዘመን ማራዘም የሚያስችል የህገ-መንግሥት ድንጋጌ ባለመኖሩ አሁን ያለዉ የመንግሥት የሥራ አስፈጻሚዉ አካል የተወሰነ የጊዜ ገደብ ተሰጥቶት በሥልጣን እንድቀጥል ተደርጎ በዚህ ግዜ ውስጥ፡ ስልጣን ላይ ያለው አስፈጻሚው አካል የእለት ተእለት የመንግስት ስራ ከማከናወንና ምርጫን ለማካሄድ ከማገዝ ውጪ ህግ ወይም አዋጅ ማውጣት፣ ማሻሻል ወይም ያሉትን ህጎች መሻር እና አዳድስ አደረጃጀትና አወቃቀሮችን መዝርጋት የለበትም፡ ብለን እናምናለን። ይህም ማለት ህገ-መንግስቱ እንዳለ ሆኖ ወይም ሳይነካ አሁን ላጋጠመን አድስና ያልተለመደ ፈተና በሁሉም ወገኖች የጋራ ስምምነት (consensus) አድስና ያልተለመደ ፖለቲካዊ መፍትሔ/Political settlement ልበጅለት ያስፈልጋል ማለታችን ነዉ። በዚህም መሠረት ያለንን ፖለቲካዊ የመፍትሔ ሀሳብ/አማራጭ እንደሚከተለዉ በዝርዝር እናቀርባለን።
ይህ የመፍትሔ ሀሳብ/አማራጭ የተመሠረተባቸዉን መሠረታዊ ምክንያቶችን መጀመሪያ ግልጽ ለማድረግ፡
 ኮቪድ-19 የ2012 ጠቅላላ ምርጫ በታቀደለት ጊዜ ዉስጥ እንዲካሄድ የማያስችል መሆኑን ስለሚናምንበት፣
 በህገመንግሥቱ አንቀጽ 9.2 ላይ በማያሻማ መልኩ እንደተቀመጠዉ፡ “ማንኛውም ዜጋ፣ የመንግሥት አካላት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ሌሎች ማኅበራት እንዲሁም ባለሥልጣኖቻቸው፣ ሕገ መንግሥቱን የማስከበርና ለሕገ መንግሥቱ ተገዢ የመሆን ኃላፊነት አለባቸው፡፡” ይላል። በዚህ እናምናለን። ላለፉት ዓመታት መሠረታዊ የመቀራረቢያ ሰነድ ሆኖ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንደ መሸጋገሪያ ድልድይ እንዲያገለግል ተስፋ የተጣለበት ይሄዉ ህገ-መንግሥት ስለሆነ እሱ ከመሠረቱ ሳይነካ ይች እንደ አገር ሆና እንዳትቀጥል ጥያቄ ዉስጥ በማይገባበት ሁኔታ ምርጫዉን ለማራዘም፣
 የኢትዮጵያ ሕዝቦችን የጋራ ጥቅምና ሀገራዊ ህልውና የሚያስከብርና የሚያራምድ የዉጭ ግንኙነት ፖሊሲ ጥያቄ ዉስጥ እንዳይገባ፣
 ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲዉ መስክ፡ በኢጋድ/IGAD, በአፍሪካ ህብረት/AU እና በተባበሩት መንግሥታት/ UN ዉስጥ ያላት ድርሻ እንዳይታገድና ይህ አሻጋሪዉ መንግሥት ህጋዊነቱ ላይ የጋራ ስምምነት እንድኖረን፣
 ሀገራዊ ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲፈጠር በፍጥነት ሀገራዊ ሰላምን የሚከላከል መንግሥት እንድኖር፣
 አሁን ሀገር እየመራ ያለዉ ፓርቲ በለዉጡ መጀመሪያ አከባቢ የገባዉን ቃል በመሸርሸር ህግና ህገ-መንግሥት አስከባሪ አካላትን ለራሱ ፖለቲካዊ ጥቅም በመጠቀም የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎችን አባላትና ደጋፊዎችን (የአመራር አባላትን ጨምሮ) በእስር ቤቶች በማጎሩ የተጣለበት ተስፋና እምነት እንደተጠበቀ አለመሆኑን ከግንዛቤ በማስገባት፣
 ባጠቃላይ አሁን ሀገሪቱን ያጋጠመዉ ፊተና መፍትሔዉ ከህገ-መንግሥቱ ዉስጥ ተፈልጎ ልገኝለት የማይችልና አድስ እንደመሆኑ በአድስ አቀራረብ በአድስና ፖለቲካዊ መፍትሔ ብቻ ልንወጣዉ የሚንችል ነዉ ብለን ስለምናምን ነዉ።
ከላይ የተዘረዘሩት ነጥቦችን በመመርኮዝ አሁን ያለዉ መንግሥት የሥራ አስፈጻሚዉ አካል (Executive body of the current Government) ለአንድ ዓመት ሥልጣኑ እንዲራዘም ሆኖ ጠቅላላ ምርጫው በግንቦት ወር 2013 ተጠናቆ አዲስ የሚመረጠው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀደም ስል በተለመደው ግዜ ስራውን እንድጀምር ማድረግ። ይህ እንዳለ ሆኖ ያሉት ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች በሚከተሉት ሀገራዊ ጉዳዮች ዉስጥ በቀጥታ ተሳትፎና ድርሻ ኖሮዋቸዉ ለሚፈለገዉ የዴሞክራሲ ግምባታም ሆነ ለሀገር ሰላምና ህልዉና ይረዳ ዘንድ ወጥ የሆነ መፍትሔ “Political conventions” መቅረጹ የግድ ይላል።
እነሱም፡
1. በዉጭ ግንኙነት አካል ዉስጥ (Council of Foreign Relation)
 To inspire domestic trust and gain international legitimacy.
2. በብሔራዊ ደህንነት (Coordinated National security council or Committee for Monitoring the Implementation of the Security Arrangements )
 ሀገር ደህንነትና ሰላም ጉዳዮች አካል ዉስጥ (በሀገር ደህንነት፣ መከላከያ፣ ፖሊስ፣) ከፖለቲካዊ ወገንተኝነት ነፃ በሆነ መንገድ ማገልገላቸዉን ለመከታተልና ብሎም በሀገር ህልውና ላይ የሚቃጣ አደጋ ቢያጋጥም የጋራ ሀላፍነት ለመዉሰድ እንዲያግዝ
 To balance the need for bureaucratic, technocratic, security and judicial expertise against the aim to limit the influence of the previous regime. To create civil order and end violence, while ensuring that all security and intelligence forces would be subject to control by the new civilian authorities.
3. የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ተቋማት (Democratic Institutions building) ዉስጥ ተሳታፊነት
 የሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ መብቶች ዋስትና የሆኑት ተቋማት ዉስጥ የተፎካካሪ ፓርቲዎችን ተሳትፎ በማሳደግ ሂደቱንና አሠራሩን የሚቆጣጠር ሥርዓት መፍጠር። (Procedural limits how the government can act, in order to prevent arbitrariness, corruption, oppression, discrimination, and the misuse of public office for personal gain)
 የባለሥልጣናትን ሥልጣን ኣለግባብ መጠቀም የሚከታተልና የሚቆጣጠር ነፃና ገለልተኛ የዳኝነት ሥርዓትና የሚዲያ ተቋማት መኖራቸዉን ለመከታተልና ለማረጋገጥ የሚረዳ አሠራር ማበጀት (To establish or protect the autonomy and authority of independent judiciaries and independent media that could hold national executives and others accountable)
4. ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር የሚረዳ ኮሚሽን
 ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር የሚረዳ የጋራ አካል በጋራ መፍጠር
5. የተራዘመዉን የጊዜ ገደብ አግባብ ባልሆነ መልኩ በመጠቀም ለሌላ ችግር እንዳይዳርገን የሚቆጣጠር ኮሚቴ
 To limit Unrealistic deadlines and attempts to move forward with the political settlement process
የእነዚህን አካላት ተጠሪነትና የአሠራር ሥርዓት በዝርዝር አዘጋጅተን የሚናቀርብ ይሆናል።
በመጨረሻም አሁን ስልጣን ላይ ያለው የፌዴራል መንግስት፣ የክልል መንግስታት፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቪክ ማህበራት እና ከሁሉም በላይ ደግሞ የአገርጡ ህዝቦች ከላይ የደረስነበትን የፖልቲካ ውሳኔ የምርጫ ህግን በሚመለከት ህግ መንግስቱን ካጋጠመው ቀውስ ሊያሻግረን እንደሚችል ስለምገነዘቡ ውሳኔያችንን ይጋራሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን።
ትብብር ለህብረ-ብሔር ዲሞክራሲያዊ ፈደራልዝም(ትብብር)
ሚያዚያ ቀን 2012 ዓም
አድስ አበባ
ከዚህ በላይ በትብብር ለህብረ ብሔር ዴሞክራሲያዊ ፌዴራሊዝም የቀረበው የመፍትሔ ሃሳብ ሰነድ አይተውት ለውይይት እንዲያቀርቡ ለዶ/ር ዐብይ አህመድ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚንስትር የተላከ ሲሆን
ለኢፌዲሪ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰብሳቢ
ለኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ
ለህዝብ ተውካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ
ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ
ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ግልባጭ ተደርጎላቸዋል

Advertisement

About advocacy4oromia

The aim of Advocacy for Oromia-A4O is to advocate for the people’s causes to bring about beneficial outcomes in which the people able to resolve to their issues and concerns to control over their lives. Advocacy for Oromia may provide information and advice in order to assist people to take action to resolve their own concerns. It is engaged in promoting and advancing causes of disadvantaged people to ensure that their voice is heard and responded to. The organisation also committed to assist the integration of people with refugee background in the Australian society through the provision of culturally-sensitive services.

Posted on May 9, 2020, in Finfinne, Information, News, Oromia. Bookmark the permalink. Leave a comment.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: