Daily Archives: June 20, 2020

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ለሲዳማ ህዝብ ታሪካዊ መልዕክት አስተላለፈ።

(ኦሮሚዲያ, 20 ሰኔ 2020) የኦሮሞ ነፃነት ግንባር(ኦነግ) ለመላው የሲዳማ ህዝብ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላለፈ።

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የሲዳማ ብሔር የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ጥያቄ በሰላማዊ ትክክለኛና ህጋዊ በሆነ መልኩ እልባት ማግኘቱን አስመልክቶ ባስተላለፈዉ መልዕክት ስኬቱ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለዉ አዉስቷል።

“ይህ ስኬት የራስንዕ ዕድል በራስ የመወሰን መብቱን ለማስከበር ለዘመናት መራራ ትግል ሲያካሄድ ለኖረው የሲዳማ ሕዝብ ታላቅና ታሪካዊ ድል ነው።”

ኦነግ በመልዕክቱ እንደገለፀዉ የሲዳማ ህዝብ የዘመናት ጥያቄ ሆኖ የቆየው ራሱን በራስ የማስተዳደር እና በክልል የመደራጀት ህገ፡መንግስታዊ ጥያቄ ከረጅም ጊዜ ትግልና መስዋትነት በኋላ የተገኘ በመሆኑ ምሳሌነቱም አስተማሪና አበረታችም ነው።

ኦነግ በመልዕክቱ እንደገለፀዉ የሲዳማ ብሔር በመሪር ትግሉ የተጎናፀፈው ይህ ድል ልክ እንደ ሲዳማ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብታቸውን ለማስከበር በመታገል ላይ ለሚገኙ ሌሎች ሕዝቦችም መልካምና ተስፋ ሰጪ ዜናም ነው ።

የሲዳማ ህዝብ ታሪካዊ በክልል የመደራጀት ጥያቄው ዛሬ እውን ሆኖ በይፋ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መምጣቱ ትልቅ ድል መሆኑን ያወሰዉ ኦነግ “ለሲዳማ ብሔር እንኳን የትግልህ የድል ፍሬ እና የታጋዮች ልጆች መስዋዕትነት ዉጤት የሆነውን ይህን ታሪካዊ ደስታ ለማጣጣም በቃህ” በማለት መጪዉ ጊዜ የዘመናት ጥማት የሆኑት ነፃነት ሰላምና ዴሞክራሲ (ፍትሃዊ አስተዳደር) የሚረጋገጡበት እንዲሆን መልካም ምኞቱን ገልጿል።

የሲዳማ ህዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር ህገ፡መንግስታዊ ጥያቄው ምላሽ እንዲያገኝ ለረጅም ጊዜያት ያለመታከት ታግሏል።

የሰላም አምባሳደር የሆነው የኦሮሞ ህዝብ ከአጎራባች እና ሌሎች ኢትዮጵያዊያን ህዝቦች ጋር ያለው ኢኮኖሚያዊ ፣ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ መስተጋብር እንዲጠናከር ከመቼውም ጊዜ በላይ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ኦነግ በዚሁ የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክቱ ገልጿል።

የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ሰኔ 11 2012 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ ፌዴረሽን አባል መንግስታት አንዱና አሥረኛዉ (10ኛዉ) ሆኖ በመዋቀር በይፋ የክልላዊ መንግስት ሥልጣኑን በመረከብ በይፋ የክልል ምስረታ ስልጣን ርክብክብ አድርጏል፡፡

የሲዳማ ህዝብ ህገ፡መንግስቱ ያጎናፀፈውን መብት በመጠቀምም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአካሄደው ህዝበ ውሳኔ መነሻ ይፋ በሆነው የድምጽ ውጤት መሠረት የራሱን ክልል ለማደራጀት የሚያስችል ድምጽ ማግኘቱ የሚታወስ ነው።

Advertisement
%d bloggers like this: