የጫልቱ ታከለ ፈተና እና ፅናት

የጫልቱ ታከለ ፈተና እና ፅናት
ጸሐፊ፡- ማሕሌት ፋንታሁን
ከአንዴም ሁለት ጊዜ የእስርን ሕይወት ተጋፍጣለች፡፡ በማዕከላዊ እና የትነቱ በማይታወቅ የእስር ቦታ የማሰቃየት ተግባር ተመሥርቶባታል፡፡ ከ8 ዓመታት በላይ ከዕድሜዋ ላይ ተቆጦ በእስር ባክኗል፡፡ ጫልቱ ታከለ፡፡ እርሷ ግን በፅናት ፈተናዋን ተወጥታለች፡፡ በእስር ቤት ውስጥ ከአስቸጋሪ ሁኔታዎች እና ክልከላዎች ጋር እየታገለች የመጀመሪያ ዲግሪዋን እስከመያዝ ደርሳለች፡፡ በዚህ ትረካ የጫልቱ ታከለን ያለፉት ዐሥር ዓመታት ጉዞ በወፍ በረር እንቃኛለን፡፡
ጫልቱ ታከለ ማን ናት?
ጫልቱ ታከለ በኦሮሚያ ክልል ሻምቡ ከተማ ነው እድገቷ። የ34 ዓመት ወጣት ስትሆን ሁለት ጊዜ የኦነግ አባል ነሽ ተብላ ታስራ በአጠቃላይ ለዘጠኝ ዓመታት በእስር አሳልፋለች። በኦሮሞ ህዝብ ላይ የሚደርሰውን ግፍ እና ሰቆቃ ስታይ በማደጓ እንዲሁም ብዙ የምታውቃቸውን ሰዎች በኢሕአዴግ ስርዓት ማጣቷ ኢሕዴግን ለመቃወም ምክንያት እንደሆናት ነገር ግን ስርዓቱን በግሏ ከመቃወም ውጪ ከኦነግ ጋርም ሆነ ሌላ ድርጅት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንዳልነበራት የምትናገረው ጫልቱ፣ መጀመሪያ የታሰረችው በግንቦት ወር 2000 ሲሆን በወቅቱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካል ሳይንስ ሁለተኛ ዓመት ተማሪ ነበረች። በቀረበባት ክስ የ12 ዓመት ፍርድ ከተፈረደባት በኋላ በአመክሮ ስምንት ዓመት ከታሰረች በኋላ ሰኔ 18/2008 ቀን ተፈታች። “ቃሊቲ ከገባሁ እና ከተፈረደብኝ በኋላ የደኅንነት ሰዎች መጥተው አናግረውኝ በስህተት እንዳሰሩኝ እና ጥፋተኛ ነኝ ብዬ ይቅርታ ብጠይቅ እንደሚፈቱኝ ሲጠይቁኝ ‘ጥፋተኛ አይደለሁም፤ ይቅርታም አልጠይቅም’ አልኳቸው” የምትለው ጫልቱ በቃሊቲ ቆይታዋ በርቀት ትምህርት ከሶስዮሎጂ ዲፓርትመንት የመጀመሪያ ዲግሪዋን ጨርሳለች።
ከተፈታች በኋላ በተማረችው ትምህርት ሥራ ለማግኘት የተለያየ ቦታ ብታመለክትም አሰሪዎች እሷን በመቅጠራቸው የሚደርስብን ቅጣት ይኖራል በሚል ስጋት ዕድሉን ሊሰጧት ስላልቻሉ ወደ ሱዳን ሔዳ ሥራ ለመሥራት ትወስናለች። ከተፈታች ከስምንት ወር በኋላ ለሥራ ወደ ሱዳን ለመሔድ ከአዲስ አበባ ተነስታ ወደ ጎንደር መንገድ ላይ እያለች እንጦጦ ኬላ ላይ በፖሊስ ተይዛ ኦነግን ለመቀላቀል ልትሔጂ ነበር ተብላ የካቲት 30/2009 ቀን በድጋሚ ታስራለች። ከአምስት ወር በላይ በፌደራል የወንጀል ምርመራ ማዕከል (‹ማዕከላዊ›) ከቆየች በኋላ የሽብር ክስ ተመሥርቶባትም ክሷን በእስር ሆና እየተከታተለች እያለ ከ11 ወር የእስር ቆይታ በኋላ መንግሥት “ለሕዝብ እና ለመንግሥት ጥቅም ሲባል” የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ የሚል ውሳኔ ባስተላለፈበት ጊዜ የሷም ክስ ተቋርጦ ተፈታለች።
እርቃን ሆኖ ስቃይ
ግንቦት 2/2000 ቀን ነበር መጀመሪያ ጊዜ የታሰረችው። የምትኖርበት ቤት መጥተው የወሰዷት ፖሊሶች የእስር ማዘዣም ሆነ የቤት ብርበራ ፈቃድ አልያዙም ነበር። ጫልቱ ስለአያያዟ ሁኔታ እና የማእከላዊ ቆይታዋ ስትናገር “የምኖርበት ቤት ፖሊሶች ሲመጡ እኔን ፈልገው ይሆናል ብዬ በፍፁም አልጠረጠርኩም። የአክስቴን ልጅ፣ የወንድሜን ሚስት፣ የቤት ዘበኛ እና እኔን ነበር ወደ ማዕከላዊ የወሰዱን። ማዕከላዊ ስንደርስ የወንድሜን ሚስት ሌሎች ሴት እስረኞች ያሉበት ክፍል ሲያስገቧት እኔን ግን ከሌሎች ሴት እስረኞች ለይተው ለብቻዬ አንድ ክፍል ውስጥ አስቀመጡኝ። ቀን፣ ማታ እና ለሊት ለምርመራ እያሉ ይጠሩኛል። የምመረመርበት ክፍል ውስጥ በአንድ ጊዜ ሰባት ስምንት እና ከዛ በላይ መርማሪዎች ይኖራሉ።

ጫልቱ ታከለ በአሁኑ ወቅት ለዘጠኝ ዓመታት ተለይታው ከነበረው ከእስር ቤት ውጪ ያለ ዓለም ጋር ለመግባባት እና ሥራ ፍለጋዋ ተሳክቶላት የቀድሞ ሕይወቷን ለመቀጠል ተግታ በመንቀሳቀስ ላይ ትገኛለች።
“ልብሴን አውልቄ እራቁቴን እንድቆም ካደረጉ በኋላ እጄን በካቴና አስረው ሰቅለውኝ ይገርፉኛል። በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ አብረውኝ ይማሩ የነበሩ አምስት ተማሪዎች ከደኅንነት አካላት ይደርስባቸው በነበረ ክትትል ብዛት እና ስጋት ጠፍተው ነበረ። በወቅቱ ደግሞ ቦሌ እና ኢምፔሪያል ኖክ ማደያዎች ላይ ቦንብ ተወርውሮ ስለነበረ፤ ከጠፉት ተማሪዎች ውስጥ አንዱ የኔ ጓደኛ በመሆኑ ‹ከሱ ተልእኮ ተቀብዬ ኢምፔሪያል ሆቴል ያለ ኖክ ማደያ ላይ ቦንብ ጥያለው፤ እንዲሁም ከኦነግ ጋር ግንኙነት አለኝ› ብዬ ቃል እንድሰጥ ነበር መርማሪዎቹ የሚደበድቡኝ። በዚህ መልኩ ለአምስት ቀናት በማዕከላዊ ከቆየሁ በኋላ አመሻሽ ላይ እቃሽን አዘጋጂ ተባልኩ። እኔም ከሌሎች ሴት እስረኞች ክፍል ሊቀላቅሉኝ ነው ብዬ አስቤ ነበረ።” ትላለች፡፡ ይሁን እንጂ ያሰበችው አልሆነም፡፡
ድብቁ “የምርመራ ቦታ”
– አራት ወር ሙሉ ፍርድ ቤት አለመቅረብ
– ኢሰብኣዊ ማሰቃየት
– ፍርድ ቤት የማያውቀው ማቆያ ቦታ መያዝ
ጫልቱ ትዝታዋን ቀጥላለች፡፡ ማዕከላዊ ብቻዋን ከታሰረችበት ውጪ ተብላለች፡፡ ከዚያም፣ “እንዳሰብኩት ሳይሆን” ትላለች፡፡ ምክንያቱም የብቻ እስሩ የቀረላት መስሏት ነበረ፡፡ “እጄ በካቴና እንደታሰረ እንዲሁም ዓይኔን በሻሽ ሸፍነው ከማዕከላዊ አስወጥተው ወደማላውቀው ቦታ ያለ ቤት ወሰዱኝ። እንደሚፈልጉት ስላላመንኩላቸው ተጨማሪ ጫና በማድረግ አሰቃይተው ለማሳመን በማለት ነበር የማይታወቅ ቦታ የወሰዱኝ። ቤተሰብ ያለሁበትን ሁኔታ አያውቅም ነበር፤ ቤተሰቦቼ ማዕከላዊ ገብተው ስለእኔ እንዳይጠይቁ ተከልክለው ነበር። ምግብ ሲያመጡልኝም ‹ጫልቱ የምትባል አናውቅም› እያሉ ቤተሰቦቼን ይመልሷቸው ነበር። እዛ ቦታ ላይ ቀንና ለሊት ስለነበረው ስቃይ መናገር ይከብደኛል” ትላለች፡፡
ጫልቱ የማይታወቅ ቤት ከተወሰደች በኋላም እጇ በካቴና እንደታሰረ ድብደባ እየተፈፀመባት ለሦስት ወር ቆይታለች፡፡
ዳግም ወደ ማዕከላዊ
ጫልቱ ወደ ማዕከላዊ ከተመለሰች በኋላ፣ ካቴናው ያረፈበት እጇ እና በድብደባ የተጎዳው ሰውነቷ እንዲያገግም በማለት ለ20 ቀን ብቻዋን ካስቀመጧት በኋላ ከሌሎች ሴት እስረኞች ጋር ቀላቀሏት። ከሌሎቹ እስረኞች ጋር ከተቀላቀለች ከ20 ቀናት በኋላ ማለትም ከታሰረች ከአራት ወር ከ20 ቀን በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወልመራ የሚገኝ የኦሮሚያ ፍርድ ቤት አቀረቧት። ቀጠሮ ተሰጥቷት ወደ ማዕከላዊ ከተመለሰች በኋላ ወልመራ ፍርድ ቤት የተሰጣት ቀጠሮ ሳይደርስ አዲስ አበባ፣ የፌዴራል አንደኛ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት እንድትቀርብ ተደረገች። ከታሰረች በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከቤተሰብም ጋር የተገናኘችው አራዳ ፍርድ ቤት ከቀረበች በኋላ ነው። ከሳምንት በኋላ መስከረም 30/2001 ቀን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀርባ የቀረበባት ክስ ደርሷታል። የዋስትና መብቷን ተከልክላ ስለነበረም ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ሆና ክሷን ስትከታተል ቆይታለች፡፡
የበኩር እስር ክሷ – “የግዛት አንድነትን መንካት”
ከዚያ ሁሉ ስቃይ በኋላ የቀረበባት ክስ የወንጀለኛ መቅጫ ሕጉን አንቀፅ 241ን ተላልፈሻል፤ (የአገሪቱን የፖለቲካና የግዛት አንድነት በመንካት የሚደረግ ወንጀል) በሚል ሲሆን፣ የቀረቡባት ማስረጃዎች:- በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ እያለች ከጓደኞቿ ጋር ሠላምታ ለመቀያየር የተለዋወጠቻቸው ኢሜይሎች፣ ማዕከላዊ ከገባች በኋላ ወደ ኢሜሏ የተላከ የሴቶችን አደረጃጀት በተመለከተ የሚያወራ ወረቀት፣ ለፖሊስ በግዳጅ የሰጠችው ቃል፣ እንዲሁም ቃል ስትሰጥ ተመልክቻለው የሚል የደረጃ ምስክር ነበሩ፡፡ ከታሰረች አንድ ዓመት ከአምስት ወር ቆይታ በኋላ (ኅዳር 8/2002 ቀን 12 ዓመት ተፈርዶባታል) የ12 ዓመት ፍርድ ተፈርዶባታል።
ከፍርድ በኋላ ይግባኝ ጠይቃ የነበረ ቢሆንም ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ያቀረበችው ይግባኝ ተቀባይነት አላገኘም። ዳኞቹ “በኦነግ አባልነት ተከሰሽ የ12 ዓመት ፍርድ ትንሽ ነው። ከዚ ወዴት እንቀይርልሽ?” ብለው ፍርዱን የካቲት 12/2002 ቀን እንዳፀኑባት ጫልቱ ትናገራለች።
ሕይወት በቃሊቲ – የሴቶች ዞን
– በአመለካከት ምክንያት መገለል
– በቤተሰብ የመጎብኘት መብትን መነፈግ
የቃሊቲ ማረሚያ ቤት ሕይወቷን ስታስታውስ፣ ጫልቱ እንዲህ እያለች ነው፡፡ “ክስ ተመስርቶብኝ ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ስመጣ የተሻለ ቦታ ይሆናል ብዬ ጠብቄ ነበረ። ነገር ግን ማረሚያ ቤቱ ለፖለቲካ እስረኞች ጥሩ አመለካከት የሌላቸው ኃላፊዎች ይበዙበታል። ከሌሎች ሴት እስረኞች ዕኩል አይደለም የሚያዩን። በጣም ብዙ በደል ያደርሱብናል። ቤተሰብ ለመጠየቅ፣ ሐኪም ቤት እና ፍርድ ቤት ስንሔድ/ስንመለስ አጃቢ ፖሊስ ለብቻችን ነው የሚመደብልን። ከእስረኞች ውስጥም የእኛን እያንዳንዷ ሁኔታ እየተከታተለ የሚነግራቸው ይመድቡብናል። የሚመደቡብን እስረኞች በኃላፊዎቹ ለመወደድ እና የተለያየ ጥቅም ለማግኘት ሲሉ የሆነውንም ያልሆነውንም ሔደው ሪፖርት ያደርጋሉ። ለምሳሌ በ2001 ለቃሊቲ ማረሚያ ቤት አዲስ በነበርኩ ጊዜ ሰሐራ በረሀ የሚል ዶክሜንተሪ ተሰርቶ በኢቲቪ ይተላለፍ ነበር። የኦነግ ወታደሮችን ከነመሪያቸው ደምስሰናል የሚል ይዘት ያለው ነበር ዶክመንተሪው እና ለእስረኞች ውሸት ነው አትዩ ብላ ከልክላ አስተባብራ ቲቪ በመዝጋት አሳምፃለች ብለው ቤተሰብ ሁለት ወር እንዳልገናኝ ተከልክያለሁ። እኔ ግን ዶክመንተሪው በሚታይበት ጊዜ ተኝቼ ነበር። ጭራሽ አላየሁትም። ሴት እስረኞች በሚሳተፉባቸው ማኅበራት እና ኮሚቴ ውስጥ መሳተፍም ሆነ መመረጥ አንችልም። ሊጠይቁን የሚመጡ ቤተሰቦቻችንን እንድናገኝ የሚፈቀድልን ከሌሎች እስረኞች ተነጥለን በምሳ ሰዐት ከ15 እስከ 30 ደቂቃ ብቻ ነው። ሌሎች እስረኞች ጠዋት እና ከሰዐት በኋላ ባለው የስራ ሰአት ሙሉ በፈለጉት ሰአት አጃቢ ሳይመደብላቸው ነው ቤተሰብ የሚያገኙት። የእኛ አጃቢዎች ቤተሰብ ሲያገናኙን ምሳ ሰዐታቸው ስለሆነ እና ከሰዐትም ደግሞ ወደ ሥራቸው ስለሚገቡ እኛን ያቻኩሉናል። ከተፈቀደችልን ደቂቃ ላይም እየሰረቁብን ብዙ ጊዜ አላስፈላጊ ፀብ ውስጥ እንገባለን” በማለት በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ኃላፊዎች ይደርስባት ስለነበረው መድሎ እና መገለል ትገልጻለች።

ጫልቱ ታከለ፡፡ ከአንዴም ሁለት ጊዜ የእስርን ሕይወት ተጋፍጣለች፡፡ በማዕከላዊ እና የትነቱ በማይታወቅ የእስር ቦታ የማሰቃየት ተግባር ተመሥርቶባታል፡፡ ከ8 ዓመታት በላይ ከዕድሜዋ ላይ ተቆጦ በእስር ባክኗል፡፡
በተጨማሪም በኦሮምኛ ቋንቋ ከቤተሰቦቿ ጋር በምታወራበት ጊዜ አጃቢዎቹ የሚያወሩትን መስማት ስላለባቸው በአማርኛ እንድታወራ ይነገራት የነበረ ቢሆንም እሷ ግን “ከፈለጋችሁ ኦሮምኛ የሚችል አጃቢ መመደብ ትችላላችሁ” ብላቸው ቤተሰቦቿን በኦሮምኛ ማናገር እንደምትቀጥል ጫልቱ ትናገራለች። በጊዜ ሒደትም አጃቢዎቿ ኦሮምኛ ቋንቋ በሚችሉ ተቀይረዋል። ከጫልቱ ጋርም ሆነ ሌሎች የፖለቲካ እስረኞች ጋር የሚታይ ሴት እስረኛ ቢሮ እየተጠራች ስለምን እንዳወሩ፣ ምን እንዳወሩ እና ሌሎች ተያያዥ ነገሮች ትጠየቃለች። አመክሮዋን እንደምትቀማ ከመንገር ጨምሮ ብዙ ማስፈራሪያዎች ይደርሷታል። በሚደርስባቸው ማስፈራሪያ እና ኃላፊዎቹ እነ ጫልቱ ላይ በሚያደርጉት የተለየ ቁጥጥር ብዙ ሴት እስረኞች ከፖለቲካ እስረኞች ጋር አብሮ ለመሆን ይፈራሉ።
“ብዙ ጊዜ ሴት የፖለቲካ እስረኞች ወደ ቃሊቲ ማረሚያ እንደገቡ ይህን ሕገ መንግሥቱን የሚፃረር እና አድሎአዊ አሠራር በመቃወም ማረሚያ ቤቱ ከሌሎች ሴት እስረኞች ዕኩል እንዲያያቸው እና እንዲያስተዳድራቸው በማለት ለፍርድ ቤት አቤቱታ ቢያቀርቡም፣ ምላሽ እንዲሰጡ ፍርድ ቤቱ የሚጠራቸው ኃላፊዎች ሁሉንም እስረኞች ዕኩል እንደሚያስተናግዱ በመግለጽ የቀረበው አቤቱታ ከእውነት የራቀ እንደሆነ አድርገው ይክዳሉ። ፍርድ ቤትም ተጨማሪ ምርመራ ሳያደርግ ጉዳዩን መፍትሔ ሳይሰጥ ይዘጋዋል። ወደ መጨረሻ አካባቢ ማረሚያ ቤቱ እንዲህ ዓይነት ክሶች ሲበዙበት ቤተሰብ የመጠየቂያ ሰዐታችንን ወደ አንድ ሰአት አራዝሞት ነበር” የምትለው ጫልቱ በድጋሚ በ2009 ቃሊቲ የገባች ጊዜም ምንም ለውጥ እንዳላየች ትናገራለች።
ትምህርት በማረሚያ ቤት
ቃሊቲ ከገባች ጀምሮ ባሉት ሁለት ዓመታት በማረሚያ ቤቱ ለታራሚዎች የሚሰጡ ሥልጠናዎችን ወስዳለች። በፀጉር ሥራ እና በእንጨት ሥራ ሥልጠናውን በብቃት አጠናቃለች። በተለይ የፀጉር ሥራ ሥልጠናውን አብረዋት ከነበሩ አብላጫ ነጥብ በማምጣት ነበር የጨረሰችው። በማረሚያ ቤት ውስጥ በሚገኘው የሴት እስረኞች ፀጉር ቤት የሚሠሩ እስረኞች የሚመረጡት በሥልጠናው ወቅት ባመጡት ነጥብ ነበረ። ሆኖም የማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች ጫልቱን በፀጉር ቤት ውስጥ ተቀጥራ እንዳትሠራ፣ የእስረኛ ኮሚቴዎች እሷን እንዳይመድቧት ትዕዛዝ ተላለፈላቸው። ኮሚቴዎቹም እንዲህ ዓይነት አድሎ ከምንሠራ በማለት ከኮሚቴነት ራሳቸውን አገለሉ። ጫልቱም በማረሚያ ቤቱ ፀጉር ቤት ውስጥ የመሥራት መብቷን ተከለከለች።
ጫልቱ ስትታሰር በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የሁለተኛ ዓመት የፖለቲካል ሳይንስ ትምህርቷን ለማቋረጥ ተገድዳ ነበር፡፡ በእስር ቤት እያለች የቀለም ትምህርቷን ለመቀጠል ብዙ ለፍታለች። ቃሊቲ ከገባች ጀምሮ ትምህርቷን በራሷ ወጪ በርቀት ለመቀጠል በተደጋጋሚ ብትጠይቅም ተቀባይነት ሳታገኝ ለዓመታት የቆየችው የፖለቲካ እስረኛ በመሆኗ ብቻ ነው። ሌሎች መማር የሚፈልጉ እስረኞች በርቀት ፕሮግራም በተለያዩ ኮሌጆች ትምህርታቸውን እንዲማሩ ይፈቀድላቸው እና ሁኔታዎችም ይመቻችላቸው ነበር። በ2005 የማረሚያ ቤቱ የትምህርት ኃላፊ የሆነው ሰው በተቀየረ ጊዜ ሴት እስረኞችን ሰብስቦ ትምህርት የመማር መብት እንዳላቸው እና እንዲማሩም አበረታትቷቸው ስብሰባው ከተጠናቀቀ በኋላ፤ ጫልቱም በድጋሚ ጥያቄዋን አቅርባለች፡፡ ማረሚያ ቤቱ በፖለቲካ እስረኞች ላይ የሚደረገውን መድሎ ያላወቀው አዲሱ ኃላፊ ትምህርቷን በርቀት የመረጠችው ኮሌጅ እንድትማር የፍቃድ ደብዳቤ ይሰጣታል። ደብዳቤው ከተሰጣት በኋላ የመማሪያ ሞጁል እንዲገባላት፣ በፈተና ቀንም ፈታኝ እንዲገባላት እና ሌሎች አስፈላጊ ሁኔታዎች እንዲሟሉላት ሌሎች ኃላፊዎችን በምትጠይቅበት ወቅት፤ ትምህርት እንድትማር መፈቀዱ ስህተት እንደሆነ በቁጭት እና በመበሳጨት ይገልጹላታል፡፡ የትምህርት ክፍል ኃላፊውም ጠርቷት “ለምን በኦነግ አባልነት ነው የታሰርኩት አላልሽኝም ነበር? ለምን ታስወቅሽኛለሽ?” ሲላት “እኔ የዛኔ ስብሰባ ሰብስባችሁ ስትነግሩን ለሁሉም እስረኛ መማር እንደሚቻል ነው የነገራችሁን። በኦነግ ለተከሰሱ እና ላልተከሰሱ ብላችሁ አለያችሁም።” የሚል ምላሽ እንደሰጠችው የምታስታውሰው ጫልቱ፣ ኃላፊው እሷ እንድትማር ፍቃድ ከሰጠ በኋላ ከነበረበት ቦታ እንዲነሳ ተደርጎ ወንዶች እስረኞች ወዳሉበት ዞን እንዲቀየር መደረጉን ትገልፃለች።
እሷ ትምህርት እንዳትማር የማይፈልጉት ኃላፊዎች መከልከል ቢፈልጉም ከሚመለከተው ክፍል ያገኘችው ፍቃድ ይዛ ፍርድ ቤት እንደምትከሳቸው ስትነግራቸው እንደሐሳባቸው ከትምህርቷ ሊያስተጓጉሏት ባይችሉም፣ በሰዐት እየከፈለቻቸው ሊፈትኗት የሚመጡትን አስተማሪዎች ረጅም ሰዐት እንዲቀመጡ እና እንዲጠብቋት በማድረግ ያንገላቷቸው እንዲሁም ያስፈራሯቸው ነበር። በዚህ ምክንያትም ፈታኞች ተቀያይረውባታል፤ ቀርተውባታል። ከማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች የሚገጥማትን ተንኮል እና ሴራ ተቋቁማ ከሪፍት ቫሊ ዩንቨርስቲ ኮሌጅ በሶሲዮሎጂ ዲፓርትመንት የመጀመሪያ ዲግሪዋን እዛው በእስር እያለች ልትጨርስ ችላለች።
በዚህ ዓይነት ሁኔታ ስምንት ዓመታትን በእስር ካሳለፈች በኋላ በአመክሮ ተፈትታ ከወደጃ ዘመዶቿ ጋር ለመቀላቀል በቅታለች፡፡
እስር እንደገና
ጫልቱ ከተፈታች ዓመት እንኳን ሳይሞላት ነበር በድጋሚ ለእስር የተዳረገችው፡፡ በሁለተኛው ስትታሰር በመጀመሪያው እስሯ የገጠማት ዓይነት የከፋ ሰብአዊ መብት ጥሰት አልገጠማትም። በመጀመሪያው እስሯ ከእስር እንደወጣች ሥራ ለማግኘት ያደረገችው ሙከራ ቀጣሪዎች በሚያድርባቸው ፍርሓት ስላልተሳካላት ተስፋ ቆርጣ ሥራ ፍለጋ ወደ ሱዳን በጎንደር በኩል ለመሔድ ጉዞ በጀመረች ቀን (የካቲት 30/2009) እንጦጦ ኬላ ላይ በደኅንነት ሰዎች የተያዘች ሲሆን ወደ ማዕከላዊ ከወሰዷት በኋላ የዛኑ ዕለት ፍርድ ቤት ቀርባለች። ለምርመራ በምትጠራበት ጊዜ “የኦነግ አባል ለመሆን ተስማምቼ ሥልጠና ለመውሰድ ወደ ኤርትራ ልሔድ ስል ነው የተያዝኩት” ብለሽ ቃል ካልሰጠሽ በሚል በስድብ፣ በዛቻ እና በጥፊ እየመቱ እያስፈራሩ ጫና ሊያሳድሩባት ጥረዋል። ሆኖም ጫናውን ተቋቁማ ለፖሊስ ያመነችበትን እውነት ብቻ እንዲጽፉ አድርጋለች። በሽብር የተጠረጠሩ ግለሰቦች ለምርመራ ከሚፈቀድበት ጊዜ በላይ ማዕከላዊ ቆይታለች። ከታሰረች ከአምስት ወር ከ17 ቀን በኋላ ነሐሴ 16/ 2009 ነው ክስ የተመሰረተባት። ክሱ ከቀረበባት በኋላ የተመሰረተባት ክስ ዋስትና ስለማይፈቅድ ቃሊቲ ሆና ክሷን እንድትከታተል ፍርድ ቤቱ ትእዛዝ በመስጠቱ በድጋሚ ወደ ቃሊቲ ገባች።
የሁለተኛ እስር ክሷ – “የኦነግ አባልነት”
በሁለተኛው እስር የቀረበባት ክስ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀፅ 7(1) ሥር የተመለከተውን (የሽብርተኛ ድርጅት አባል መሆን) ተላልፈሻል ተብላ ነው። የቀረቡባት ማስረጃዎች:— የመረጃ እና ደኅንነት ኤጀንሲ በጽሑፍ ያቀረበው የተጠለፈ የስልክ ልውውጥ ሪፖርት እንዲሁም ለፖሊስ የሰጠችው ቃል ነው።
የቀረበባትን ክስ እንድትከላከል ከተነገራት በኋላ የመከላከያ ማስረጃዎቿን እንድታሰማ የተሰጣትን ቀጠሮ በመጠባበቅ ላይ እያለች መንግሥት የፖለቲካ እስረኞችን በምኅረት እና ክስ በማቋረጥ እንዲለቀቁ ባስተላለፈው ውሳኔ መሠረት የካቲት 7 ቀን 2010 ክሷ ተቋርጦ ከእስር ወጥታለች።
“ችሎት ደፋሪዋ” ጫልቱ
በሁለተኛው እስሯ ወቅት፣ በቃሊቲ ሆና ክሷን እየተከታተለች ሳለ፣ ኅዳር 28/2010 ቀን ችሎቱ የዐቃቤ ሕጉን ማስረጃዎች በመቀበል የቀረበባትን ክስ ተከላክላ ነጻ እንድትወጣ ብይን አሳለፈ፡፡ ይህን ብይን ስትሰማም ያልጠበቀችው ስለነበረ “ከደኅንነት ቀረበ የተባለው ሪፖርትም ሆነ የሰጠሁት ቃል ኤርትራ ስለመሔዴ የሚያወራው ነገር በሌለበት ሁኔታ ክሱን የሚያስረዳ ማስረጃ ሳይኖር ተከላከሉ ብላችሁ ብይን መስጠታችሁ አሳዝኖኛል። ከኢሕአዴግ ፍርድ ቤት ምንም አንጠብቅም። ወደፊትም ፍትሕ እንደማናገኝ ነው የምናስበው።” ብላ በመናገሯ ችሎት ደፈርሽ ተብላ የ500 ብር ቅጣት ተወስኖባት ነበር፡፡ ከእስር ክሷ ተቋርጦ ስትወጣ ግን ቅጣቱም አብሮ ተረሳ፡፡
ከእስር መልስ – ድሮ እና ዘንድሮ
መጀመሪያ ከእስር እንደወጣች ከጥቂት የቅርብ ቤተሰቦቿ እና ጓደኞቿ በስተቀር ከእስር በመውጣቷ ደስታቸውን የገለጹላት ሰዎች አልነበሩም። ከመጀመሪያው ሁለት ዓመት ልዩነት በሌለው የሁለተኛ ጊዜ እስሯ ስትፈታ ግን ወደ ትውልድ አገሯ ሻንቡ ሳትደርስ ጀምሮ በሚገኙ ከተሞች ሕዝቡ እሷን እና ሌሎች ተፈቺዎችን በደስታ ወጥቶ ተቀብሏቸዋል። ሻንቡ ከመድረሷ በፊት በሚገኙ ከተሞችም ሆነ ሻንቡ ከተማ ስታዲየም የተደረገላቸው አቀባበልም ደማቅ፣ አስደሳች እና ያልጠበቀችው እንደነበር የምትናገረው ጫልቱ፤ ለደረሰባት የሰብአዊ መብት ጥሰት ማካካሻ የተወሰደ የሕግ፣ የገንዘብ ወይም የሞራል ካሳ የለም።
ጫልቱ ታከለ በአሁኑ ወቅት ለዘጠኝ ዓመታት ተለይታው ከነበረው ከእስር ቤት ውጪ ያለ ዓለም ጋር ለመግባባት እና ሥራ ፍለጋዋ ተሳክቶላት የቀድሞ ሕይወቷን ለመቀጠል ተግታ በመንቀሳቀስ ላይ ትገኛለች።
=============